News

የጃክ ማ ፋውንዴሽን የአፍሪካ የሥራ ፈጣሪ ጀግኖች ተወዳዳሪ

BBC News

አይቲ እና የጤና ባለሙያዎች ጥምረት የፈጠሩበት የዶ/ር ውልታ ሶፍትዌር በጃክ ማ ፋውንዴሽን ውድድር ከመጨረሻዎቹ ሃያ ተወዳዳሪዎች ውስጥ ገብቷል።

ዶ/ር ውልታ ለጃክ ማ ፋውንዴሽን ለውድድር የቀረቡት አባይ ኮኔክትድ ሄልዝ ሪከርድ (አባይ ሲ.ኤች.አር) በሚሰኘው ድርጅታቸው በኩል በሰሩት ሶፍትዌር አማካኝነት ነው።

አባይ ኮኔክትድ ሄልዝ ሪከርድ የተሰኘው ድርጅት ከተጀመረ ሦስት ዓመት መሆኑን የሚናገሩት ዶ/ር ውልታ፤ ሲጀምሩት በጣም ቀላል የሆነ፣ አፍሪካ ውስጥ የሚጠቅም፣ የዓለም አቀፍ ደረጃን የሚያሟላ ሶፍትዌር ለመስራት አቅደው መሆኑን ይናገራሉ።

ከዛሬ ሦስት ዓመት በፊት ለዚህ መነሻ ምክንያት የሆናቸው ደግሞ የታካሚዎችን፣ የሐኪሞችን እና የሆስፒታሎችን ችግር ማየታቸው መሆኑን ይገልፃሉ።

የሕክምና ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር ውልታ በተያዩ የሕክምና ተቋማት ውስጥ ለታካሚ ካርድ የሚወጣበት ሥርዓትን አስተዋሉ።

አንድ ታካሚ ካርዱን ከጣለ አዲስ ካርድ ይወጣለታል። በዚህ የተነሳ የቀደመ የሕክምና ታሪኩ ከአሁኑ ጋር አይናበብም። የታካሚው ስም ቢሳሳት የሕክምና ታሪኩን የያዘው ዶሴ አይገኝም።

ከዚህ ሁሉ ደግሞ የታካሚው ታሪክ የሚሰፍረው በወረቀት ላይ ነው። ታካሚው በተለያዩ ስፍራዎች፣ በተለያዩ ሐኪሞች ስለሚታከም ዶክተሮች የቀደመ የሕክምና ታሪኩን ለመረዳትና ለህመሙ ፍቱን ህክምና ለመስጠት ፈተና ይሆንባቸዋል።

በዚህ ወቅት የጤና ባለሙያዎች ከዚህ በፊት ታክሞ እንደሆነ ይጠይቃሉ።

ታካሚው በትምህርት የገፋም ሆነ ፊደል ያልቆጠረ ሐኪሞች መረጃ ለማግኘት ሲጠይቁት በሚገባ የማስረዳት ተግዳሮት መኖሩን ዶ/ር ውልታ ያነሳሉ።

የተሰጡ መድኃኒቶች የተደረጉ ህክምናዎችን ታካሚው ሙሉ በሙሉ ለማስረዳት እንደሚቸግር የሚናገሩት ዶ/ር ውልታ፤ “ስለዚህ መረጃ በሚገባ ካልተደራጀ ዶክተሩንም፣ ሆስፒታሉንም፣ ፋርማሲውንም፣ ላቦራቶሪውንም ሁሉንም ያስቸግራል” ይላሉ።

ታካሚ የሕክምና እርዳታ ፈልጎ ወደ ሆስፒታል በሚመጣበት ወቅት ሆስፒታሉ በአግባቡ የተደራጀ የመረጃ ሥርዓት ከሌለው በአግባቡ ለመርዳት እንደሚቸገር የሚገልፁት ዶ/ር ውልታ፤ እርሳቸው በዚህ ቴክኖሎጂ በተመነደገበት ዘመን አንድ ነገር በማድረግ የመረጃ አያያዝ ሥርዓቱን ማስተካከል እንደሚችል በማሰብ ወደ ሥራ ገቡ።

ሥራውን ሲጀምሩ ግን ብቻቸውን አልነበሩም፤ አብረዋቸው አስር ዓመት የሰሩ ስምንት ጓደኞቻቸውን ሰብስበው “እኔ የጤና ባለሙያ ነኝ፤ እናንተ ደግሞ የአይቲ እስቲ ቀላል፣ በየትኛውም ስፍራ የሚያገለግል፣ በእንግሊዘኛ ቋንቋ የሚሰራ ሶፍትዌር ፍጠሩ” እንዳሏቸው ያስታውሳሉ።

የጓደኞቻቸው የመጀመሪያ መልስ “አይቻልም” የሚል ነበር።

ለዚህ ደግሞ ምክንያታቸው ጤና በውስጡ ብዙ ነገር ማካተቱ ነበር። የላቦራቶሪ፣ የፋርማሲ፣ የአልትራሳውንድ ወዘተርፈ ክፍሎች መኖራቸው ሥራውን ከባድ አደረገው።

ከዚያ በኋላ ኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎች ተሰባስበው በሁለት ዓመት ውስጥ የዶ/ር ውልታን ራዕይ ወስደው እውን አደረጉት።

የማይክሮሶፍት የአፍሪካ ቢሮ ሰዎች ሶፍትዌሩን ባዩበት ወቅት መደነቃቸውን ዶ/ር ውልታ ይናገራሉ። ለምን?

በቅድሚያ ለሁሉም እንዲስማማ ሆኖ መሰራቱ፣ ቀጥሎ ደግሞ በአፍሪካውያን በመሰራቱ ብለውናል።

ሶፍትዌሩ በአሁኑ ጊዜ በአዲስ አበባ ቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ ባሕር ዳር በፈለገ ሕይወት እንዲሁም ደሴና ሌሎች ሆስፒታሎች እየገባ መሆኑን ተናግረዋል።

ለሥራቸው ስም ሲያወጡም አባይ ያሉት “አባይ ደም ስራችን ስለሆነ፣ የሕክምና መረጃም ደማችን በመሆኑ ነው” ይላሉ።

ዶ/ር ውልታ ከኢትዮጵያ እንዲሁም ከአፍሪካ አገራት ውጪ በደቡብ እስያ አገራትንም እንደሚያውቁ ይናገራሉ። “ሶፍትዌሩ በእኛ አገር ብቻ ሳይሆን በእነዚህ አገራትንም ይሰራል። የሰሩት ደግሞ ኢትዮጵያውያኖች ናቸው በዚህም እኮራለሁ” ብለዋል።

ስንጀምር ስምንት ነበር አሁን ስድሰት ነን ከወሎ ዩኒቨርስቲ ጋር በቅርበት እንሰራለን፤ የሰው ኃይል ድጋፍ ያደርጉልናል። በደቡብ ወሎ ያሉ የሕክምና ተቋማትን ለማጠናከር በሚሰሩት ሥራ አብረናቸው እንሰራለን ሲሉ ይናገራሉ።

ዶ/ር ውልታ እና አጋሮቻቸው የሰሩት ሶፍትዌር መረጃዎች እንዳይጠፉ ዲጂታላይዝ እንዲያደርግ፣ ለታካሚው የሚታዘዙ የላቦራቶሪ የፋርማሲ እንዲሁም ሌሎች ትዕዛዞች በአግባቡ ተሰንደው እንዲቀመጡ ያደርጋል።

በተጨማሪም በአፍሪካ ውስጥ በየሆስፒታሉ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያ ስለማይገኝ ሆስፒታሎች በራሳቸው የአሰራር መንገድ የህክምና ባለሙያው እንደፈለገው እንደ አለበት ተጨባጭ ሁኔታ መቀየርና መጠቀም እንዲችል የሚያደርግ ነው።

ዶ/ር ውልታ ይህንን ሥርዓት ሲሰሩ በሁለት መልክ ማደራጀታቸውን ይናገራሉ።

አንደኛው ደንበኛው ከፈለገ መረጃውን ክላውድ [ከየትም ቦታ ሊደረስበት በሚችል የኮሚፒውተር መረጃ ቋት] ላይ እንዲቀመጥለት፣ አይ አልፈልግም የሚል ከሆነ ደግሞ በእራሱ ሰርቨር ላይ ማስቀመጥ ይችላል።

በኢትዮጵያ ውስጥ ሥራ በጀመሩባቸው ሆስፒታሎች የታካሚዎች መረጃ የተቀመጠው በድርጅቱ ሰርቨር ውስጥ መሆኑን የሚጠቅሱት ዶ/ር ውልታ መረጃው ኢንክሪፕትድ [ምስጢራዊነቱ በተጠበቀ ሁኔታ የተዘጋጀ] መሆኑን ይገልፃሉ።

ሁሉም የሕክምና ክፍል በራሱ የይለፍ ቃል በመግባት የሚመለከተውን መረጃ ብቻ ማየት እንደሚችል፣ የታካሚውም ምስጢር በዚህ መልክ እንደሚጠበቅ ያስረዳሉ።

መረጃን ክላውድ ላይ ለማስቀመጥ ጠንካራ ኢንተርኔት ግንኙነት እንደሚያስፍለግ ገልፀው፣ ወደፊት አንድ ሆስፒታል ጠንካራ ኢንተርኔት ግንኙነት ካለው ክላውድ ላይ ማስቀመጥ እንደሚችል ይጠቅሳሉ።

ዶ/ር ውልታ የሰሩት ሶፍትዌር በየትኛውም የሕክምና ተቋም ውስጥ እንዲሰራ ተደርጎ መሰራቱን በመግለጽ፤ በገጠሪቱ የአገሪቱ ክፍሎች ባሉ የጤና ጣቢያዎችም ሆነ በሪፈራል አልያም ስፔሻላይዝድ ሆስፒታሎች ውስጥ ያለችግር መጠቀም እንደሚቻል ያብራራሉ።

ዶ/ር ውልታ ከዓለም የቴና ድርጅት ዳይሬክተር፣ ከቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆርጅ ቡሽ እና ከሌሎች ጋር
https://www.bbc.com/amharic/news-54019064?fbclid=IwAR3eRnmM01d7IOAySGfvXSCOD75jMDuJklFX4aeh7FmdB1KsHo0qxBlnFBQ_aem_AVVqqE4VovU-CSiQJX6eVjVxr4V2Lbgb1CTH0zZYqBK3PK1c_33IHkKgT0U1PPi9alrYi_9nD0Zs5xmGSBnzRNXG